Back to Front Page


Share This Article!
Share
ወንጀለኛ እና አርበኛ ተምታታብን

ወንጀለኛ እና አርበኛ ተምታታብን

(ክፍል ሁለት እና የመጨረሻ)

ሰዒድ ከሊፋ 08-22-18

የሐገሪቱን ህዝብ ለድህነት እና ለኋላ ቀርነት የዳረጉትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመገንዘብ በቅድሚያ ለትግል የተነሳው ያ ትውልድ፤ የሐገሪቱንና የህዝቦችዋን ችግር ለመፍታት ያስችላል ብሎ ያስቀመጠውን መሥመር ይዞ የታገለ ቢሆንም፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የነበረው አስተዋፅዖ ውስን ነው፡፡ የዚያ ትውልድ አካል የሆኑ ቅን ወጣቶች በተሳሳተ የትግል መስመር ተጉዘው ብዙዎቹ እሳት ውስጥ የገባ ቅቤ ሆነው ጠፍተዋል፡፡ ህዝቡንም ለከፋ ጨፍጫፊ ስርዓት ጥለውት ተበታትነዋል፡፡

ከዚያ ትውልድ የትግል ስልት አንዳንድ ስህተቶችን እና አንዳንድ የአመለካከት ችግሮችን በማረም፤ ከረጅምና መራራ የትጥቅ ትግል በኋላ ለዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት የጣለው የፌዴራላዊት ኢትዮጵያ መስራች ትውልድም፤ ለምስጋና እና ለውግዘት የሚያበቁ ሥራዎችን ሰርቶ፤ አሁንም ለስርዓቱ መጠናከር እየተጋ ላለው ባለወርተራ ትውልድ መንገድ የለቀቀ ይመስላል፡፡ በርግጥ ሥራው ከወቀሳ ባያድነውም አምባገነኑን ስርዓት በመገርሰስ፤ ህገ መንግስታዊ ስርዓትን ለመለማመድ የምንችልበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት በኢህአዴግ ጥላ ሥር የተሰባሰበው የለውጥ ኃይል በአባላቱ፣ በደጋፊዎቹ እና በአጋሮቹ ድጋፍ አዲስ ገዳና ለመተለም፤ በወረሳቸው መጥፎ ዕዳዎች ሸክም ትከሻው እንደጎበጠ ሐገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመውሰድ ቀን ከሌሊት እየተጣጣረ ይገኛል፡፡

Videos From Around The World

ዛሬ በፖለቲካ መድረኩ ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑት የዚያ ትውልድ አባላት፤ በኢህአዴግ ዙሪያ እና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ተሰልፈው፤ ከቀደመው ዘመን በተለየ መንፈስ ለመስራት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ በሁለቱ ጎራም ከሚገኙት ፖለቲከኞች ውስጥ ብዙዎቹ በአፈና ስርዓት ባህል ትውፊት ውስጥ ያደጉ በመሆናቸው፤ ብዙ ፈተና የሚገጥመው ትግል ውስጥ ገብተዋል፡፡ የዚያ ትውልድ አባላት፤ በአፈና ስርዓት አድገው፤ የስርዓቱን ችግር ተገንዝበው፣ በፖለቲካውና በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በመሳተፍ የአፈና ስርዓቱን ቢጥሉም፤ አሁንም ከአፈና ባህል ውርስ ራሳቸውን በመነጠል፣ የገዛ አስተሳሰባቸውን በመታገል፣ አዲስ ባህል በመገንባት፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት እና ስርዓቱን ለማጠናከር ብዙ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ አንዳንዶች ከራሳቸው ጉድለቶች ጋር እየታገሉ፤ ራሳቸውን እና አካባቢያቸውን በአብዮት ሃዲድ ውስጥ አስገብተው የተሳካ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፤ በአዲሱ ስርዓት ውስጥ በራሳቸውና በአካባቢያቸው ላይ አዲስ ለውጥ ለማምጣት መታገል እንደሚገባቸው ያልተገነዘቡ አንዳንዶች የአፈና ስርዓት ባህል እያሸነፋቸው እና በየአጋጣሚው እያገረሸባቸው የለውጥ እንቅፋት ሆነው ይታያሉ፡፡

ቀደም ሲል እንዳልኩት፤ በትክክል የሚያስብ ሰው እንዲህ አያደርግም፡፡ ይህ ችግር የሚመነጨው በትክክል ካለማሰብ ነው፡፡ በትክክል ያለማሰብም ምንጩ፤ ተጨባጨን ነገር በትክክል ካለማወቅ ነው፡፡ በትክክል ያለማሰብ እና ተጨባጨን ነገር በትክክል አለማወቅም፤ ትክክል አለማድረግን ያመጣል፡፡ ትክክል ያለማድረግ አንዱ መገለጫም፤ የህግ የበላይነትን አለማክበር እና ሁከት መቀስቀስ ነው፡፡ የህግ የበላይነት በማይከበርበት ሁኔታ የሚሰራ ሥራም ጥፋት እንጂ ልማት ሊሆን አይችልም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የሩቅ ትናንት ህይወቱን በሐዘን፤ የዛሬ ህይወቱን በጽናት እና የነገ ህይወቱን በተስፋ በመመልከት፤ ራሱን በራሱ የሚያርም ስርዓት ለማፅናት እየተጋ እና ነገን በተስፋ በማየት ወደ ብሩህ ዘመን ለመጓዝ ጥረት እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት፤ በትግል የለኮሰውን የተስፋ ችቦ የሚያከስም ነውረኛ የወንጀል ድርጊቶችን እየተመለከተ ዝም ሊል አይችልም፡፡ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመኮንኖች የምረቃ ስነ ስርዓት በተገኙበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ነጻነት ይከበር ማለት ህግ አይኑር፣ ስርዐተ አልበኝነት ይንገስ ማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በተለያየ ምክንያት የሰዎች ህይወት በየቀኑ ሲጠፋ እየተመለከተ ዝም ብሎ ለማለፍ አይችልም፡፡

ደርግ ቀይ ሽብርን የፈፀመው የህግ የበላይነትን ባለመቀበሉ ነበር፡፡ የስነ- ስርዓት እና የወንጀል ህጉ የፈለገው ሆኖ፤ ደርግ ረበሹኝ የሚላቸውን ወጣቶች ራሱ ባወጣው ህግ እንኳን ጉዳያቸው እንዲታይ እና በዛው መንገድ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጠው አድርጎ ቢሆን ኖሮ የህግ የበላይነትን አክብሯል ማለት ይቻለን ነበር፡፡ የደርግ ስርአት የዳኝነት ነፃነት የተከበረበት ሥርዓት ቢሆንም ባይሆንም፤ ይህ በራሱ ትልቅ ሥራ ሆኖ በተቆጠረለት ነበር፡፡

ዛሬ ለበርካታ ዓመታት በተጓዝንበት መንገድ ሄደን ለውጥ አናመጣም፡፡ መንግስት እኔ ያልኩህን ካልፈፀምክ እና ጥያቄህን ለማስፈፀም ጠብመንጃ ካነሰህ፤ እንደ መንግስት አይቀጡ ቀጥቼ አንበረክክሃለሁ ከሚል የእልህ ስሜት ተላቆ፤ ያነሳችሁን ጠብመንጃ አስቀምጣችሁ፤ ጠብመንጃ በማንሳት የአመጽ ጎዳናን መከተል ስህተት መሆኑን በይፋ ገልፃችሁ፤ በሰላማዊው የፖለቲካ መድረክ ለመታገል ከወሰናችሁ ወይም ወደ ሰላማዊ መድረክ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆናችሁ፤ ክስና ቅጣት ሳልል የሰላም አማራጮችሁን ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ በማለት፤ ጠብመንጃ ካነሱ የፖለቲካ ቡድኖች ጋር ድርድር ለማድረግ ሲሞክር፤ በዚህ ሀገር ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ፍፁም አዲስ እና አብዮታዊ እርምጃ ነው፡፡

ይህ ብቻ በዚህ ሀገር አዲስ ነገር እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የፖለቲካ ጥያቄን በጠብመንጃ እና በኃይል የማወራረድ ፖለቲካዊ ባህል እየተቀየረ፤ የፖለቲካ ጥያቄን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በማወራረድ ፖለቲካዊ ባህላችን በአዲስ እሴት እየተተካ መምጣቱን የሚያስገነዝብም ነው፡፡ ነገር ግን መቀየር ያለበት መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አስተሳሰባቸውን በዴሞክራሲያዊ እሴት ማረቅ ይገባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ ኢህአዴግ ጠብመንጃ አንስተው ከሚዋጉት ወገኖች ጋር እየተነጋገረ፤ ደረቅ ወንጀል ለሰሩ ወገኖች በየዓመቱ ምህረት እየሰጠ፤ እኛ በሰላማዊ መንገድ እየታገልን ከምናገኘው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር አለመፍቀዱ ትክክል አይደለም የሚል ወቀሳ በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እና እርሱ በሚመራው መንግስት ላይ ይሰነዝሩ ነበሩ፡፡ መንግስት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ቡድኖች ጋር ብቻ ሳይሆን ጠብመንጃ አንስተው ከሚዋጉት ጋር እየተነጋገረ የእኛን የውይይት ጥያቄ አልቀበልም ይላል ሲሉ የሚወቅሱም ነበሩ፡፡ ዛሬ እንዲህ ያለ ሮሮ አይሰማም፡፡ መንግስት በብዙ ተቀይሯል፡፡

በእርግጥም ዛሬ ጠብመንጃ አንስቶ ከሚወጋው ኃይል ጋር ለመወያየት የደፈረ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ የነበረውን የፖለቲካ ባህል እና ልምድ በመተው እና ሥነ- ምግባራዊ የበላይነት በመያዝ መንፈሳዊ ጀግንነት የተላበሰ እርምጃ ከመንግስት አይተናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በፖለቲካው መድረክ ከሚፎካከረው የፖለቲካ ድርጅት ጋር ብቻ ሳይሆን ጠብመንጃ ካነሳ ኃይል ጋር ለመወያየት አገር አቋርጦ የሚጓዝ መሪ እና መንግስት አግኝተናል፡፡

ቀደም ሲልም በኢህአዴግ ጥሪ አቅራቢነት እና ጥሪውን አክብረው በመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተባባሪነት የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ በሚል የሚታወቅ እና ፓርቲዎቹ በጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክር የሚያደርጉበት መድረክ አለ፡፡ ይህ የፓርቲዎቹ የጋራ መድረክ በአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም የተዘጋጀን የሥነ-ምግባር ደንብ መመሪያው ያደረገ መድረክ ነው፡፡ በዚህ የጋራ መድረክ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነ አንድ የፖለቲካ ፓርቲም መኖሩን እናውቃለን፡፡ ይህ የፖለቲካ ፓርቲም አንድነት - መድረክ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው፤ መድረክ ወደ ጋራ መድረኩ ለመምጣት ፈቃደኛ ያልነበረው ኢዴፓ ከሚባል ፓርቲ ጋር ቁጭ ብዬ አልደራደርም በሚል ነበር፡፡ ይህንም ምክንያት ስንሰማ አዝነን ነበር፡፡ ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ ከምንታገለው እኛ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ አይደለም እያለ የሚወቅስ ፓርቲ እንዴት እንዲህ ይላል ብለን ነበር፡፡ ይህን ነገር የማነሳው፤ ለማሳጣት ሳይሆን ለትምህርት ብቻ ነው፡፡ ኢህአዴግ እኛ በሰላማዊ መንገድ የምንታገለው ወገኖች የምናቀርብለትን የውይይት ጥያቄ ሳይቀበል፤ ጠብመንጃ ካነሳው ወገን ጋር ይነጋገራል የሚል ክስ እያቀረበ፤ ኢዴፓ ከሚባል ፓርቲ ጋር ቁጭ ብዬ አልደራደርም የሚለው ነገር ማንሳቱስ ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ የዚህ አቋም አንድምታ ከታየም ፀረ- ዲሞክራሲያዊ ትርጉሙ የጎላ ነበር፡፡

በአንድ በኩል፤ መሣሪያ አንስቶ ከሚዋጋው ኃይል ጋር ያለ ውጭ ኃይል ሽምግልና እና ግፊት በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ፈቃደኛ የሆነ መንግስት፤ በሌላ በኩል እከሌ የተባለ ፓርቲ ባለበት መድረክ ቁጭ ብዬ አልደራደርም የሚል የፖለቲካ ፓርቲ አይተናል፡፡ ኢህአዴግ ጠብመንጃ ካነሳ ኃይል ጋር ሲነጋገር፤ ሌላው ኢዴፓ ከሚባል ፓርቲ ጋር ቁጭ ብዬ አልደራደርም ይል ነበር፡፡ አንደኛው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል መሠረታዊ እሴት በሆነና ችግሮችን በውይይትና በመመካከር የመፍታት ጥረትን የሚደግፍ ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው፡፡ ሌላኛው፤ እኔ ከማልወደው ፓርቲ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ አልወያይም የሚል የዴሞክራሲ እሴትን የሚፃረር አቋም ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጠብመንጃ ካነሣ ኃይል ጋር ቁጭ ብሎ ለመደራደር ፈቃደኛ የሆነ እና በሁሉም ረገድ ጠንካራ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ መንግስት መታየቱ የሚያመለክተው ዕድገት ነው፡፡ ፖለቲካዊ ክስተትን ለማሽሟጠጥ ታስቦ የተፈጠረ ምጸት ይመስል፤ እከሌ የተባለ ፓርቲ ባለበት ጤረጴዛ ተቀምጬ አልራደርም የሚል አቋም የሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት መታየቱ ደግሞ ትኩረት የሚሻ ቀሪ ሥራ መኖሩን ያመለክታል፡፡

አማራጭ ሐሳብ የማቅረብና የመደመጥ ዕድል ልትነፍጉን አይገባም፡፡ የጋራ ለሆነችው ሀገራችን እኛም የምናበረክተው አስተዋፅዖ ተገቢ ግምት ሊሰጠው ይገባል የሚል የፖለቲካ ድርጅት፤ እኔም አማራጭ አለኝ ብሎ የተቋቋመ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ በሚገኝበት የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ መድረክ ለመገኘት አልፈልግም ማለት አይገባውም ነበር፡፡ ይህ አቋም ፍፁም የተሳሳተ አቋም መሆኑን ለመረዳት አለመቻሉ፤ ይህን የተሳሳተ አቋም ከሁለት ዓመት በላይ ይዞ መዝለቁ፤ በዚህች ሀገር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጠናከር ለሚሹት ብቻ ሳይሆን፣ ለፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችም አሳፋሪ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ በውስጣቸው የሚነሱ የአቋም ልዩነቶችን በምን መንገድ ነው የሚያስተናግዱት የሚል ጥያቄም በህዝቡ ዘንድ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢዴፓ ሀሳብ እኔ ባለሁበት መድረክ እንዲሰማና በሀሳብ ትግል እንዲሞግተኝ መፍቀድም አልፈልግም የሚል ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚጻረር አቋም ነበር፡፡

ለማይወዱት ሐሳብ የመደመጥ ዕድል መስጠት የማይፈቅድ አቋም ፀረ- ዴሞክራያዊ አቋም ነው፡፡ ሐገራችን ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት እንድትሸጋገር እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች መታረም አለባቸው፡፡ መንግስት ከያዘው ፖሊስ የተለየ አማራጭ ፖሊሲ አለን ከሚሉ ወገኖች ጋር መነጋገርና መወያየት አለበት ሲሉ ወቀሳ የሚያቀረቡ ወገኖች፤ ከእነርሱ የተለየ ፕሮግራም የያዘው እና የተለየ ፖሊሲ ከሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት፤መድረክ የሚባል ፓርቲ በሚገኝበት መድረክ ለመነጋገር አልፈልግም የሚል አቋም ሊወስድ አይገባም፡፡

ይሁንና ባለፉት ዓመታት የታዩ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህልን የሚያመለክቱ አበረታች አዝማሚያዎችም ነበሩ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መድረክ መፍጠራቸው፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ በደል ቢደርስባቸውም በዚህ መድረክ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸው፤ የጋራ መድረኩ የሚገዛበትን የሥነ-ምግባር ደንብ ማጽደቃቸው፤ የጋራ መድረኩ አባላት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት የደም ስር ለሆነው የመወያየትና የመደራደር እሴት አክብሮት ማሳየታቸው፤ እንደኛ ዓይነት የፖለቲካ ባህል ላለው ህዝብ የእድገት ምልክቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ሌላ፤ በ1993 ዓ.ም በኢህአዴግ አመራሮች (በተለይም በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች) ውስጥ የከረረ የአቋም ልዩነትና አንጃ በተፈጠረ ጊዜ፤ አመራሮቹ የመከላከያ ኃይሉን ወደ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ለመሳብ አለመሞከራቸው፤ ከሁሉም በላይ ሠራዊቱ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን አውቆ፣ ተረድቶና አክብሮ ዳር መቆሙ፤ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን አለመረጋጋት ሰበብ አድርጎ ወደ ፖለቲካ ትግሉ ሜዳ ለመግባት አለመቃጣቱ፤ እንዲሁም በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ማግስት ሰላማዊ የሥልጣን መተካካት ተደርጎ ሥርዓቱ ሳይንገጫገጭ መጓዝ መቻሉ፤ በዳዴም ሆነ በእርምጃ የስርዓቱን እየተጠናከረ መሄድ እና ተቋማዊ መሠረት መያዝ ፍንጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እነዚህን ነገሮችን የማነሳው ለዕድገት ጉዞ ለእንዲህ ያሉ ትናንሽ ስኬቶችን ዕውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆንኑ ስለማምን እና እንደ ህብረተሰብ ያለብን ጠቅልሎ ከመጣል እና ጠቅልሎ ከማንሳት ዓመል ችግር ሊያወጣን ይችላል ከሚል እምነት ነው፡፡ አሁን ያለንን ሰፊ የለውጥ ዕድል በማስተዋል መጠቀም ይኖርብናል፡፡

 

Back to Front Page